Amhara women association .AWA, [11/25/2025 7:34 AM]
ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን የሚጸየፍ ትውልድ መገንባት ይጠበቃል።
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ በማንኛውም ሁኔታ ጾታን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊ ጥቃትን፣ ትንኮሳን እና ማስፈራራትን ለመከላከል የሚደረግ ንቅናቄ ነው።
ይህንን ጥቃት ለመከላከል የሚደረግ ዘመቻ “የነጭ ሪቫን ቀን” በሚል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ይታሰባል፡፡
ይህ ዘመቻ በየዓመቱ ከኅዳር 16 ጀምሮ ለተከታታይ 16 ቀናት ይካሄዳል። ኅዳር 16 ዓለም አቀፍ በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት የማስወገድ ቀን ተደርጎም ይከበራል። ታኅሣሥ 01 ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን ነው።
በእነዚህ ቀናት ውስጥ በዓለም ዙሪያ ጾታዊ ጥቃትን የሚቃወሙ፣ ግንዛቤ የሚፈጥሩ እና ለተጎጂዎች ድጋፍ የሚውሉ የተለያዩ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ።
የነጭ ሪቫን ቀን በወንዶች እና በተለይ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመቃወም ቃል የሚገቡበትም ነው። ነጭ ሪቫን ማድረግ ወይም አርማውን መያዝ ልዩ መልዕክትም አለው።
በዘመቻው ወንዶች ደረታቸው ላይ ነጭ ሪቫን አድርገው ሲንቀሳቀሱ በሴቶች ላይ ጥቃት ላለመፈጸም፣ ጥቃት አድራጊዎችን ላለመደራደር፣ በሴቶች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ዝም ላለማለት ቃል ኪዳን እንደገቡም ይቆጠራል።
ወንዶች የችግሩ አካል ብቻ ሳይኾኑ የመፍትሔውም አካል እንዲኾኑ ማበረታታት፣ ጤናማ እና መከባበር የሰፈነበት ግንኙነትን ማስተማር፣ ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲጸየፍ የሚያደርግ ነው።
በዓሉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ1991 ጀምሮ ሲከበር ቆይቷል፡፡ ዘንድሮም በዓለም ለ34ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።
👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇
Amhara women association .AWA, [11/25/2025 7:35 AM]
በአማራ ክልል”ጥቃትን የማይታገስ ማኅበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ከዛሬ ጀምሮ እየተከበረ ነው።
የአማራ ሴቶች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ገነት ወንድሙ የነጭ ሪባን ቀን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የሚጸየፍ ትውልድ ለመገንባት ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሴቶችን መብት እና ደኅንነት በማስጠበቅ ሚናውን እንዲወጣ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያግዝ መኾኑንም ተናግረዋል። የማኅበረሰቡን ንቃተ ህሌና ለማሳደግ ሰፊ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ነው ብለዋል።
በ16ቱ ቀናት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄን ለማከናዎን ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም በስፋት እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በንቅናቄ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እየተከናወነ መኾኑንም አመላክተዋል።
ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለጾታዊ ጥቃት የተዳረጉ ሴቶችንም መልሶ ለማቋቋም የማደራጀት እና በገቢ ማስገኛ ሥራዎች በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለጹት በክልሉ የተፈጠረው የተራዘመ ግጭት እና አለመግባባት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እያባባሰ እና ለከባድ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ሰብዓዊ ቀውሶች እየዳረገ ነው። ይህንን ለመከላከልም መላው ሕዝብ ሰላም እንዲመጣ መረባረብ ይገባዋል ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ማኅበረሰቡ ወደ ቀደመ እሴቱ እንዲመለስ በማድረግ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
ሚዲያዎችም በየደረጃው ጥቃትን የሚጸየፍ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ግንዛቤ በመፍጠር በኩል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

