ባሕር ዳር: መስከረም 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር ከዞን ቅርንጫፎቹ ጋር የ2016 በጀት ዓመት ሥራዎቹን ገምግሞ የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን የሴቶች ማኅበር የቦርድ ሠብሣቢ ሙሉእመቤት ድጋፌ ማኅበሩ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል ጨምሮ በምጣኔ ሃብት እና በማኅበራዊ ዘርፍ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል እና ለመቅረፍ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡ በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ጉዳቶች መካከል ጾታዊ ጥቃት፣ መደብደብ እና በገጠር ሴቶች መሬት መቀማትን የጠቀሱት ወይዘሮ ሙሉእመቤት ማኅበሩ ችግሩን ለመከላከል እና ለመፍታት ገለልተኛ ኾኖ ይሠራል ብለዋል፡፡
ለወትሮውም ቢኾን በሴቶች ላይ ጫናዎች አሉ ያሉት ወይዘሮ ሙሉእመቤት በግጭት ጊዜ ደግሞ የበለጠ ተጋላጭ ይኾናሉ ስለኾነም ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም መሥራት ይገባዋል፤ እየሠራም ነው ብለዋል፡፡
ሰላም በመደፍረሱ የሚኖረውን ችግር ለመቀነስ ብሎም ለመከላከል በማኅበራቸው አባላት በኩል እንደሚሠሩም ነው የገለጹት፡፡
ማኅበሩ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሴቶችን ሁለንተናዊ ችግር ለመቀነስ እንደሚሠራ ገልጸው ሌሎችም የሴቶችን ችግር ለመፍታት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ማኅበር አሥተባባሪ አገርሰው ታደሰ ማኅበሩ ከተቋቋመ ከ25 ዓመት በላይ እንደኾነው ተናግረዋል፡፡ ሴቶችን በምጣኔ ሃብት፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
ሴቶች የተለያዩ ችግሮች ይደርሱባቸዋል ያሉት ወይዘሮ አገርሰው ማኅበሩ የሚፈልገው ከችግሮቻቸው እንዲወጡ፣ አደባባይ ወጥተው ሃሳባቸውን እንዲገልጹ፣ ችግራቸውን እንዲከላከሉ የግንዛቤ ፈጠራ እና የማጠናከር ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
ማኅበሩ ሲቪክ ማኅበር እንደመኾኑ ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ኾኖ በመሥራት ሴቶች ተደራጅተው መብት እና ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር እንዲታገሉ ማድረግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የሴቶችን ጥቃት በመከላከል እና ከችግሩም በኋላ ድጋፍ በማድረግ እየሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት፡፡
ሰላም ከሌለ የበለጠ ተጎጅዎቹ ሴቶች መኾናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ አገርሰው ለሰላሙም የመፍትሄ አካል በመኾን መሥራት እንደሚገባ ነው የመከሩት፡፡
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላሙ እንዲመጡ ሴቶች ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው ለሰላም መሥራት እንደሚገባቸው እና ለአሉቧልታም ተጋላጭ መኾን እንደሌለባቸው ነው የተናገሩት፡፡
መደፈርም ኾነ እገታ ሴቶችን የበለጠ ተጎጅ ማድረጉን እና በሰላም እጦትም የወሊድም ኾነ ሌሎች የሕክምና ክትትላቸውን ማድረግ ስለማይችሉ ለሰላም አጥብቀው መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር ምክትል ዳይሬክተር ሁሉአየሽ አወቀ ማኅበሩ የተቋቋመበት ዓላማ የሴቶችን የሥነ ተዋልዶ ጤና መብቶችን በማስከበር፣ የሴቶችን ጥቃት በመከላከል እና በሕግ እንዲያልቅ በማድረግ፣ በጦርነት ወቅት ጉዳት እንዳይደርስ እና ከደረሰ በኋላም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በማኅበረሰቡ በኩል አሁንም ድረስ የሴቶችን ችግር ያለመገንዘብ ውስንነቶች አሉ፤ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
ጦርነት በተፈጠረ ቁጥር የሴቶች ጥቃት እንደሚበዛ ከሰሜኑ ጦርነት ትምህርት ተወስዶ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በመቀበል ድጋፍ እየተደረገ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭትም የሴቶችን ችግር እንዳከፋው ጠቅሰው ችግሩን ለመከላከል እና ለመቀነስ መረጃ እየተጠናቀረ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የሴቶች ጥቃት እንዲቀንስም ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
አሁን ላይ ሴቶች በቤት ውስጥ እና በመንገድ ላይ እየወለዱ እና ለሞት አደጋ እየተጋለጡ ነው ያሉት ወይዘሮ ሁሉአየሽ የወሊድ አገልግሎት አቅርቦቱም አለመኖሩን ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን እና ተጋላጭ የኾኑትን ሴቶች ጨምሮ ከሰላሙ ተጠቃሚ ለመኾን በበጎ ፈቃደኛ ሴቶች አማካይነት እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት፡፡
የሴቶች ተጠቃሚነት የሚኖረው ሰላም ሲኖር በመኾኑ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን ለሰላም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ እናቶች ልጆቻቸውን እንዲመክሩ እና ሰላም እንዲፈጠርም እየተሠራ ስለመኾኑ ነው የተናገሩት፡፡