በኮምቦልቻ ከተማ ቦርከና ክፍለ ከተማ የሚገኙ የአማራ ሴቶች ማህበር አባላት በጋራ በመደራጀትና የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ የራሳቸውን የገቢ ማስገኛ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ እንደሚገኝ ተገለጸ።
የአድማስ ራሳገዝ የሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወ/ሮ ፋጡማ ኢማም እንደገለጹት ስብስቡ የጀመረው በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች በኢኮኖሚ ለመደገፍ “ዊ አክሽን” ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው የይሉናል መጀመሪያ ላይ በ120 ሴቶች የተጀመረው ይህ እንቅስቃሴ፣ ሴቶቹ በየቡድናቸው እንዲደራጁና የሥነ-ልቦና እንዲሁም የኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ የተጀመረ እንደሆነ ያወሱት ሊቀመንበሯ ሴቶቹ መጀመሪያ ላይ በቡድን ተደራጅተው እያንዳንዳቸው የ1,000 ብር መነሻ ካፒታል በማግኘት ወደ ሥራ ገብተዋል። በዚህም ዳቦና እንጀራ በመጋገር እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ በመሸጥ ራሳቸውን መርዳት እንደጀመሩ ያስታውሳሉ ከዛም አራት የሴቶች ቡድኖች ተዋህደው የቁጠባ ማህበር በመመሥረት እርስ በእርስ በመበዳደርና በመረዳዳት እስከ 600,000 ብር የሚደርስ ቁጠባ ማከማቸት በመቻላቸው በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ የእንጀራና የዳቦ ማምረቻ ማህበር ማቋቋም ችለዋል። በአሁኑ ወቅት የማህበሩ አጠቃላይ ቁጠባ 1.5 ሚሊዮን ብር ደርሷል።
ከኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ጋር በተደረገ ቅንጅት 348 ካሬ ሜትር ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን፣ አስተዳደሩ በ7 ሚሊዮን ብር ወጪ የሥራ ቦታ (ሼድ) ግንባታ አከናውኖላቸዋል።
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት 80 አባላት ያሉት ሲሆን፣ በቀን 15,000 እንጀራዎችን ለመጋገር አቅዷል። በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ለ400 ሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ስራውን ለማስፋት ግብ ይዟል።
ምንም እንኳን ማህበሩ ውጤታማ ቢሆንም፣ አሁንም በዋናነት የገበያ ትስስር ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ወይዘሮ ፋጡማ ጠቁመዋል። “አንድ ሴት በቀን 200 እንጀራ ካልሸጠች ተጠቃሚ ልትሆን አትችልም፤ ስለዚህ ምርታችንን ለሆቴሎችና ለተለያዩ ተቋማት ለማቅረብ የገበያ ትስስር ያስፈልገናል” በመሆኑም የሚመለከተው አካል የገበያ ትስስር እንዲፈጥርላቸው መልክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም፣ ሴቶች ተደራጅተው ሲሠሩ እውቀትና ጉልበትን በማቀናጀት ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ የገለጹት ሊቀመንበሯ ሌሎች ሴቶችም በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉና በጋራ ተደራጅተው በአኮኖሚ ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።





